ጥቅምት 8/2018 ዓ.ም
ኬብሮንሂል አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ
የመመሥረቻ ጽሑፍ
ጥቅምት 8/2018 ዓ.ም
ምዕራፍ አንድ
አንቀጽ አንድ
የኩባንያው ስም
ኩባንያው “ኬብሮንሂል አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ” ተብሎ ይጠራል፡፡
አንቀጽ ሁለት
የኩባንያው አድራሻ
ኬብሮንሂል አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ዋና መስሪያ ቤት አዲስ አበባ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ደብረወርቅ የንግድ ማዕከል 10ኛ ፎቅ የቤት ቁጥር 10-01/02/03 ነዉ፡፡
የአክሲዮን ማህበሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፎችን እንደየአስፈላጊነቱ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ሊከፍት ይችላል፡፡
አንቀጽ ሶስት
የባለአክሲዮኖች ስም፣ አድራሻ፣ ዜግነትና የአክሲዮን ይዞታ ዝርዝር
እኛ ስማችን፣ ዜግነታችን፤ አድራሻችን እና የአክስዮን ድልድላችን ከዚህ በታች የተገለጸው የኬብሮንሂል አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ (ከዚህ በኋላ ማህበር” ተብሎ በሚጠራው”) መሥራች ባለአክሲዮኖች በአዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ህግ (ከዚህ በኋላ “የንግድ ሕግ” ተብሎ የሚጠራው) እና በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1164/2012 እና በየወቅቱ በሚወጡ አግባብነት ባላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ከዚህ በታች ‘‘ማህበሩ’’ ተብሎ የሚጠቀሰውን ኬብሮንሂል አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም አ.ማ አቋቁመናል፡፡
አንቀጽ አራት
አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ዓላማና ተግባር
አነስተኛ ፋይናንስ ተቋሙ የሚከተሉትን በሙሉ ወይም በከፊል ሊያከናውን ይችላል፤
- አነስተኛ ፋይናንስ ተቋም ዋና ዓላማ ገንዘብ መሰብሰብና በገጠርና በከተማ በግብርና፤ በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስኮች እንዲሁም በሌሎች መሰል ስራዎች ለተሰማሩ ሰዎች ጣርያው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሚወሰን ብድር መስጠት ይሆናል፡፡
- የፈቃደኝነት፤ የጊዜ ገደብ፤ የግዴታ ቁጠባዎችን እንዲሁም የተለያዩ የቁጠባ አማራጮችን ለወጣቶች፤ ለሴቶች፤ ለአርሶ አደሮች፤ ለነጋዴዎችና ለሌሎች ማቅረብ፤
- በአዲስ አበባ እና በሌሎች የማህበሩ ቅርንጫፎች ባሉባቸው አከባቢዎች በተለይም በከተማ ዙሪያ ለሚኖሩ ነዋሪዎች እና ገጠራማ አከባቢ በግብርና እና በሌሎች ሥራዎች እንዲሁም ጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ መስኮች ወይንም በሌሎች ምርታማ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚያካሂዷቸውን ገቢ የሚያስገኙ ፕሮጄክቶችን ፋይናንስ በማቅረብ ማገዝ፤
- በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከፈሉ የሃዋላ ሰነዶችን ማውጣትና መቀበል፤
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት አነስተኛ የመድን ስራ መስራት፤
- ዓላማቸው ገቢ ማስገኘት የሆነ እንደ ግምጃ ቤት ሰነዶችን እና ሌሎች የአጭር ጊዜ የንግድ ወረቀቶችን ብሔራዊ ባንክ በሚወስነው መሰረት መግዛትና መሳተፍ፤
- ሥራውን የሚያከናውንባቸውን ሕንፃዎች ጨምሮ ማናቸውንም የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት በባለቤትነት መያዝ፣ መንከባከብና ለሌሎች ማስተላለፍ፤
- በከተማና በገጠር በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ መስኮች ወይንም በሌሎች ምርታማ ተግባራት ላይ ለተሰማሩ ሰዎች የሚያካሂዷቸውን ገቢ የሚያስገኝ ፕሮጀክቶች በማማከር ማገዝ፤
- ለደንበኞች የአመራር፣ የገበያ፣ የቴክኒክና አስተዳደራዊ ምክር መስጠትና በነዚህም መስኮች አገልግሎቶች ለማግኘት እንዲችሉ ማገዝ፤
- ለጥቃቅንና ለአነስተኛ የንግድ ስራዎች ወይም መሰል ምርታማ ተግባራት ዓላማ የሚውል ገንዘብን የማስተዳደር ሥራ መስራት፤
- የፋይናንስ ኪራይ አገልግሎት በካፒታል ዕቃ ኪራይ በንግድ ስራ አዋጅ ቁጥር 103/1990 እና የካፒታል ዕቃ ኪራይ ንግድ ስራ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 807/2005 መሰረት ለተከራዮች መስጠት፤
- የወኪል ባንኪንግ አገልግሎት መስጠት፤
- ከወለድ ነፃ አነስተኛ የፋይናንስ ሥራ አገልግሎቶችን ለሚፈልጉ ሰዎች መስጠት፤
- ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት፤
- ለአርሶ አደሮች፣ለጥቀቅንና አነስተኛ ንግድ አንቀሳቃሶች በካፒታል ንብረት ሊዝ ንግድ አዋጅ ቁ.103/1990 እና የካፒታልዕቃ ንግድ ስራ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 807/2005 መሰረት የፋይናስ ሊዝ አገልግሎት መስጠት፡፡
- ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው በሚያወጣቸው መመሪያዎች በሚወሰኑ ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች እንደ አስፈላጊነቱ መሰማራት፡፡
አንቀጽ አምስት
የማህበሩ ካፒታል
- ጠቅላላ የማህበሩ የተፈረመ ካፒታል ብር 302,520,000 (ሶስት መቶ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሃያ ሺ ብር) ሆኖ በጠቅላላ ጉባኤ ዉሳኔ እና ካፒታል ገበያ በሚያወጣዉ መመሪያ መሰረት በየጊዜ ልጨምር ልቀንስም ይችላል፡፡
- ከተፈረመው የአክሲዮን ካፒታል ውስጥ የተከፈለ የአክሲዮን መጠን በብር 113,078,842.89 (አንድ መቶ አስራ ሶስት ሚሊዮን ሰባ ስምንት ሺ ስምንት መቶ አርባ ሁለት ብር ከ 89/100 ሳንቲም) ነው፡፡
- የተፈረመ የአክሲዮን እያንዳንዳቸው ብር 1000 (አንድ ሺህ) ዋጋ ባላቸው 302,520 (302,520,000 ብር) መደበኛ አክሲዮኖች የተከፋፈለ ነው፡፡
- ቀሪው የተፈረመ እና ያልተከፈለ ካፒታልን በሚመለከት አክሲዮን ማህበሩ በንግድ መዝገብ ከተመዘገበበት እለት አንስቶ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተከፍሎ መጠናቀቅ አለበት፡፡
- አክሲዮን አይከፋፈልም
አንቀጽ ስድስት
የአክሲዮን አለመከፋፈል
- ካንድ በላይ ሰዎች በጋራ የአክሲዮን ባለቤት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሰል ሁኔታዎች ውስጥ በመብታቸው ተጠቃሚ ለመሆን አንድ ሰው መወከል ይኖርባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን የጋራ ወኪል ባልሾሙ ጊዜ ማኅበሩ ለአንድ አክሲዮን የጋራ ባለቤት የሚሰጠው ማስታወቂያ ወይም መግለጫ ለቀሪዎቹ የአክሲዮኑ የጋራ ባለቤቶች ጭምር እንደተሰጠ ይቆጠራል፡፡
አንቀጽ ሰባት
የአክሲዮን አይነቶች
- ማህበሩ ተመሳሳይ ዋጋ ያላቸው የተመዘገቡ ተራ አክሲዮኖች ይኖሩታል፤
- የአክሲዮን ድርሻዎች በባለአክሲዮኖች ስም እንዲመዘገቡ ይደረጋል፤
- ማህበሩ ለአምጪው የሚከፈሉ አክሲዮኖችን አያወጣም፤
አንቀጽ ስምንት
የአክሲዮን ባለቤትነት የምስክር ወረቀት
-
- ባለአክሲዮኑ ከፈረመው የአክሲዮን ድርሻ 1/4ኛ ወይም ከዚያ በላይ ክፍያ በሚፈፅምበት ጊዜ የአክሲዮን ምስክር ወረቀት እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡
74
አንቀጽ ዘጠኝ
ክልከላዎች
ማህበሩ ከብሔራዊ ባንክ በጽሑፍ ፈቃድ እስካልተሰጠው ድረስ ከዚህ የሚከተሉትን ቀጣዮቹን ተግባራት ማስፈጸም አይፈቀድለትም፡፡
- ኩባንያውን ለመሸጥ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር ለማዋሃድ ወይም በማንኛውም ሁኔታ የኩባንያው ቢዝነስ ወይም ተግባራት ተጽዕኖ ውስጥ የሚከት አሰራር ወይም ስምምነት መፈረም
- ከሌላ መደበኛ የቢዝነስ አሰራር ውጭ በሆነ መንገድ የማህበሩን ንብረቶች በከፊል ወይም በሙሉ ማስተላለፍ ወይም ማስወገድ፤
- በኪሳራ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር የማህበሩን ካፒታል መቀነስ፤
- የተሻሻለውን የመመስረቻ ጽሁፍ ማስመዝገብ፤
- ፈቃድ ያገኘበትን ስም መለወጥ፤
- ከተፈቀደለት አካባቢ ውጭ መሥራት፤
- በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ከተቀመጠው ገደብ ውጭ በፋይናንስ ተቋማት ወይም የፋይናንስ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ወይም በመሰል የንግድ መስኮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ፡፡
አንቀጽ አሥር
ዳይሬክተሮችን የሚመለከት ብድር ወይም ዋስትና
በንግድ ሕጉ አንቀጽ 307 መሠረት የተመለከተዉ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ መመስረቻ ጽሁፍ ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ብድር መስጠት ወይም የቦርድ አባላት ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ላለባቸው ግዴታዎች ዋስ መሆን ወይም ንብረቱን በዋስትና ማስያዝ ይችላሉ፡፡
አንቀጽ አስራ አንድ
የአደራጆች ልዩ ጥቅም
በኢትዮጵያ ንግድ ህግ 1243/2013 ንዑስ አንቀጽ 253 (1) እና 254 (5) መሠረት የአደራጅ አባላት ጥቅምን በተመላከተ ተቋሙ ትርፋማ ከሆነበት ዓመት አንስቶ ለተከታታይ ሶስት (3) ዓመታት ድረስ ከአክስዮን ማህበሩ ከተጣራ ትርፍ ድርሻ ላይ 20% ይከፈላል፡፡
አንቀጽ አስራ ሁለት
ስለ ትርፍ
- የማህበሩ የተጣራ ትርፍ የሚባለው የማህበሩ ጠቅላላ ወጪዎች እንዲሁም የአላቂ ንብረቶች መተኪያ ገንዘብና የእርጅና ቅናሽ ሒሳብ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ከተቀነሰ በኋላ የሚገኘው ትርፍ ነው፤
- የሚከፋፈል ትርፍ ከሂሳብ ዓመቱ ትርፍ ላይ የቀደሙት አመታት ወጪዎች፣ተከፋዮችና ኪሳራዎች ካሉ ከተቀነሱ በኋላ በሒሳብ ዓመቱ ትርፍ ላይ በፊት ታስበው ያልተከፋፈሉ ትርፎችን እና ሌሎች ተጨማሪ ገቢዎችን እና በልዩ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔ ከመጠባበቂያ ወጪ እንዲከፈል የፈቀደውን ማንኛውንም ገንዘብ በመጨመር የሚገኝ ትርፍ ነው፡፡
- የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔም ለትርፍ ተካፋይ የሚሆኑት ገንዘቦች ከየትኛው የመጠባበቂያ ገንዘብ ላይ እንደሚወስዱ ማመልከት ይኖርበታል፡፡
አንቀጽ አስራ ሶስት
የትርፍ አመዳደብ እና ክፍፍል
- የዳይሬክተሮች ቦርድ የተጣራ ትርፍ ክፍፍል ምክረ ሀሳብን ለባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በማቅረብ እንዲፀድቅ ያደርጋል፡፡ መሰል የትርፍ ክፍፍል ከመከናወኑ በፊት ህጋዊ መጠባበቂያ ገንዘብ እና ሌሎች በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚቀርቡ መጠባበቂያ ፈንዶች ሊቀናነሱ ይገባል። ይህም በባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ታይቶ የሚፀድቅ ይሆናል፡፡ ከላይ የተመለከቱት የትርፍ ክፍፍል አሰራሮች በህግ አስገዳጅ ገደብ ከሌለ በስተቀር በዚህ መመሥረቻ ጽሑፍ መሰረት ለባለ አክሲዮኖች እንዲከፋፈል ይደረጋል፡፡
- የልዩ ሕግ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ከተጣራው ትርፍ ላይ ወደ መጠባበቂያ ገንዘብ ከተዘዋወረ በኋላ ቀሪ በማህበሩ ባላቸው የተከፈለ አክሲዮን ካፒታል ድርሻ ልክ ይሆናል፡፡
- የኩባንያው የፀደቀ የሂሳብ ሚዛን ላይ ካለው በተፃራሪ የሚፈፀም የትርፍ ክፍፍል እና እንደ ሐሰተኛ ትርፍ ተቆጥሮ በወንጀልና በፍትሐብሔር ህጋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡
- የትርፍ ክፍፍል ቀን እና አጠቃላይ ሁኔታው በባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
አንቀጽ አስራ አራት
በአስቸጋሪ ጊዜያት የትርፍ ክፍፍል ገደቦች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚጠይቀው መሠረት የማህበሩ ዋና ገንዘብና የማህበሩ የካፒታል መጠባበቂያ በቂ በአልሆነበት ሁኔታ፣ በማህበሩ የተከፈለ ካፒታል ላይ ያሉ ችግሮች ሳይወገዱና የካፒታል ወጭዎች ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ሳይሆኑ ማህበሩ የትርፍ ክፍያ (ዲቪደንድ) ለባለአክሲዮኖች መክፈልና ከትርፉ ማናቸውንም ዓይነት የማስተላለፍ ተግባራትን አይፈፅሙም፡፡
አንቀጽ አስራ አምስት
የባለአክሲዮኖች መብት እና ግዴታ
የባለአክሲዮኖች መብት
- እያንዳንዱ ባለአክሲዮን ከተጣራው ዓመታዊ ትርፍ እንዲሁም ማህበሩ በፈረሰ ጊዜ ከሚቀረው የተጣራ ንብረት ድርሻ የማግኘት መብት አለው፤
- በመመስረቻ ጽሁፉ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በስተቀር የትርፍ ድርሻና ማኀበሩ ሲፈርስ ከተጣራው ንብረት የሚገኘው ድርሻ ባለአክሲዮኑ ለማህበሩ ዋና ገንዘብ በከፈለው መጠን ይታሰባል፤
- ለእያንዳንዱ አክሲዮን ድምጽ የመስጠት መብት ይሰጣል፤ ለባለአክሲዮኑ ድምጽ የሚሰጠው ክብደት አክሲዮኑ በማኀበሩ ዋና ገንዘብ ውስጥ የሚወክለውን መጠን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት፤
- የማኀበሩን ዋና ገንዘብ ለመጨመር በጥሬ ገንዘብ ለመሸጥ የወጣ አክሲዮኖች በሚኖርበት ጊዜ እያንዳንዱ ባለአክሲዮን በማህበሩ ባለው አክሲዮን ድርሻ መጠን በቅድሚያ የመግዛት መብት ይኖረዋል፤
- በዚህ አንቀጽ ን/አንቀጽ (4) የተመለከተው መብት በንግድ ሕጉ ከአንቀጽ 448 እስከ 457
ባሉት ድንጋጌዎች መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
የባለአክሲዮኖች ግዴታ
- ባለአክሲዮኖች በዚህ መመስረቻ ጽሁፍ እና ለሌሎች አግባብነት ላላቸው ህጎች ተገዥ ይሆናል፡፡
- የባለአክሲዮኖች ኃላፊነት/ግዴታ ለማህበሩ ቃል የገቡትን መዋጮ በመክፈል የተወሰነ ነው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ወሳኝ ድምጽ ያለው ባለ አክሲዮን በንግድ ሕጉ አንቀጽ 295 መሰረት ከዚህ በታች ከተራ ቁጥር 3-8 ከተመለከቱት አንዱን ፈጽሞ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል፤
- የማህበሩን፣ የባለአክሲዮኖችን ወይም የማህበሩን ገንዘብ ጠያቂዎችን ጥቅም ጉዳት ላይ የሚጥል ሕገ-ወጥ ድርጊት ሆን ብሎ መፈፀም፤
- የማህበሩን ንብረት ከባለአክሲዮኑ ንብረት ጋር መቀላቀል፤
- የማህበሩን እና የባለአክሲዮኑን ማንነት አለመነጣጠል፣
- ማህበሩን ለግል ወይም ለሶስተኛ ወገን ዓላማና ጥቅም እንደሽፋን መጠቀም፤
- ስለማህበሩ የፋይናንስ አቋም የማህበሩ ገንዘብ ጠያቂዎችን ሊያሳስት የሚችል መረጃ ሆን ብሎ ማውጣት፤
- ከገበያ ዋጋ ባነሰ ክፍያ ወይም አግባብ ካለው የማህበሩ አመራር ውሳኔ እና እውቅና ውጪ የማህበሩን ሀብት ለራሱ ወይም ለሦስተኛ ወገኖች የግል ጥቅም ማዋል፤ ወይም በሕግ ከሚፈቀደው በላይ የትርፍ ክፍያ መፈፀም፡፡
አንቀጽ አስራ ስድስት
ቀሪ ዋጋቸው ላልተከፈለ አክሲዮኖች ስለሚኖር ኃላፊነት
- የአክሲዮን ባለይዞታዎች አክሲዮኑ ቀደም ሲል ተላልፎላቸው የነበረ ሰዎች እንዲሁም አክሲዮኑን ከማህበሩ ለመግዛት የፈረሙ ሰዎች ቀሪ ዋጋቸው ላልተከፈለ አክሲዮኖች ዋጋ ለማህበሩ በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ ናቸው፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) ስር የተደነገገው ቢኖርም፣ ማንኛውም አክሲዮን ለመግዛት የፈረመ ወይም ባለአክሲዮን የነበረ ሰው ባለቤትነቱን ያስተላለፈ እንደሆነ ካስተላለፈበት ቀን ጀምሮ ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ላልተከፈለው ቀሪ ገንዘብ ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡
- ባለአክሲዮኖች ለመግዛት ያመለከቱትን የአክሲዮን ድርሻ አሟልተው በአንድ ዓመት ውስጥ ካልከፈሉ በቀሪው የአክሲዮን ዋጋ ላይ 12% ወለድ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡
- የማህበሩ አባል ቀሪውን ገንዘብ እንዲከፍል የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ዋጋቸው በሙሉ ያልተከፈለ አክስዮኖችን በሐራጅ መሸጥ ይችላል፣ በሐራጅ የተሸጡት አክሲዮኖች ተሰርዘው ሌሎች አዳዲስ አክሲዮኖች ለገዥው ይሸጣሉ፡፡
- ገዥ ባለመገኘቱ ምክንያት አክሲዮን መሸጥ ካልተቻለ ተጨማሪ ኪሳራ ካለ መጠየቅ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ አክሲዮን ለመውረስና ለአክሲዮኑ አስቀድሞ የተከፈለውን ገንዘብ ለማስቀረት የዳሬክተሮች ቦርድ ሊወስን ይችላል፡፡
- ቀሪ ዋጋቸው ያልተከፈለ አክሲዮኖች ውርስ እንዲሆኑ በተወሰነበት የሂሳብ ማጠቃለያ ዓመት ውስጥ ያልተሸጡ እንደሆነ አክሲዮኖቹ ተሰርዘው ዋና ገንዘቡ በአክሲዮኖቹ ላይ በተጻፈው ዋጋ መጠን መቀነስ አለበት፡፡
- የገንዘብ መክፈያው ጊዜ ያሳለፈ ባለአክሲዮን በጉባኤ ላይ ድምጽ የመስጠት መብት ያጣል፡፡
አንቀጽ አስራ ሰባት
የባለአክስዮኖች መዝገብ
- የአክሲዮን ማህበሩ የባለአክሲዮኖችን መዝገብ በዋናው መሥሪያ ቤት መያዝ አለበት፤ መዝገቡ በወረቀት ወይም ለረጅም ዘመን የሚቆይ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መያዝ ይቻላል፡፡
- መዝገቡ ባለአክሲዮኖችን ስም፤ አድራሻ፤ ዜግነት፤ በአክሲዮኖችን ብዛትና መለያ ቁጥር፤ የተከፈለውን የገንዘብ መጠንና ባለአክሲዮኖቹ የተመዘገቡበትን ቀን መያዝ አለበት፡፡
- ባለአክሲዮኖችና የሚመለከታቸው የመንግስት መሥሪያ ቤቶች መዝገቡን በነፃ መመልከት ይችላሉ፡፡ ባለአክሲዮን ያልሆነ ሌላ ሰው መዝገቡን ማየት የሚችለው ለዚህ ተብሎ ማህበሩ የወሰነው የአገልግሎት ክፍያን ሲፈፅም ነው፡፡
- ማንኛውም ሰው የተወሰነውን የአገልግሎት ክፍያ ሲፈፅም የመዝገቡን ግልባጭ ወይም አጭር የተውጣጣ ጽሁፍ እንዲሰጠው ማህበሩን መጠየቅ ይችላል፤ ማህበሩ ጥያቄው በቀረበ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ግልባጩን ወይም በአጭር የተውጣጣውን ጽሁፍ ለጠያቂው መሰጠት አለበት፡፡
- ጥቅም ካለው ማንኛውም ሰው ወይም ከባለአክሲዮ ጥያቄ ሲቀርብለት አግባብ ያለው የመንግስት አካል በመዝገቡ አጻጻፍ ላይ የተፈጠረ ስህተት እንዲታረም ማድረግ ይችላል፡፡
- የአክሲዮን መዝገቡ ዝርዝር በትክክል ባለመጻፍ ምክንያት ለሚደርስ ማንኛውም ጉዳት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በአንድነትና በተናጠል ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡
78
አንቀጽ አስራ ስምንት
አክሲዮን ማስተላለፍ
በንግድ ህጉ አንቀጽ 276 ላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ባለአክሲዮኖች አክሲዮን ሲያስተላልፉ ወይም በውክልና ሲሰጡ የሚከተሉት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፡፡
- የአክሲዮን ድርሻዎች ያለ ምንም ገደብ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ይተላለፋሉ፤
- አንድ አክሲዮን ማስተላለፍ በአክሲዮን መዝገብ ላይ እስካልሰፈረ ድረስ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡
- ማንኛውም የአክሲዮን ማስተላለፍ በጽሑፍ ሊከናወን የሚገባው ሲሆን አሰራሩም የዳይሬክተሮች ቦርድ በየጊዜው በሚወስነው አኳኋን ይደረጋል፡፡
ምዕራፍ ሁለት
የማኅበሩ ጉባኤዎች
አንቀጽ አስራ ዘጠኝ
የማኀበሩ ጉባኤ ጥሪ
- ጠቅላላ ጉባኤያት የሚደረጉት እንደ ነገሩ ሁኔታ በዳይሬክተሮች ቦርድ፤ ኦዲተሮች፤ ሒሳብ አጣሪዎች ወይም ፍርድ ቤት ናቸው።
- መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በየአመቱ የሚከናወን ሆኖ ይህም አመቱ ተጠናቆ ባሉት 6 ወራት ጊዜ ውስጥ በዳይሬክተሮች ቦርድ ወይም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በኦዲተሮች የሚጠራ ይሆናል።
- ከማህበሩ ዋና ገንዘብ ውስጥ ቢያንስ አስር በመቶ ድርሻ ባላቸው ባለአክሲዮኖች ጥያቄ የቀረበላቸው እንደሆነ፤ ኦዲተሮች ጠቅላላ ጉባዔ እንዲሰበሰብ ጥሪ ማድረግ አለባቸው።
- አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ በሕሳብ አጣሪዎች ወይም በፍርድ ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ሊደረግ ይችላል፡፡
አንቀጽ ሃያ
የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ማስታወቂያ
- የመደበኛ ወይም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ ላይ ከስብሰባው ቀን 24 (ሃያ አራት) ቀናት አስቀድሞ እንዲታተም ይደረጋል፤
- የጉባዔው የጥሪ ማስታወቂያ የማህበሩን ስምና ዓይነት፤የማህበሩን ዋና ገንዘብ፣የምዝገባ ቁጥር፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚገኝበትን ቦታ፤ የስብሰባውን ጊዜና ቦታ እንዲሁም ለስብሰባው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን መያዝ አለበት።
አንቀጽ ሃያ አንድ
ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ በድጋሚ የሚደረግ የመደበኛ ጉባኤ ጥሪ
ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ መሰብሰብ ሳይችል የቀረ እንደሆነ ሁለተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲሰበሰብ የሚደረገው ጥሪ የመጀመሪያው ጉባዔ በተጠራበት አኳኋን እና የጊዜ ገደብ ነው፡፡
አንቀጽ ሃያ ሁለት
ምልዓተ ጉባዔ ባለመሟላቱ በድጋሚ የሚደረግ የአስቸኳይ ወይም የልዩ
ጉባዔ ጥሪ
አስቸኳይ ወይም ልዩ ጉባዔ አስፈላጊው ምልዓተ ጉባዔ ባለመሟላቱ ምክንያት ሳይሰበሰብ የቀረ እንደሆነ ሁለተኛ ስብሰባ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ሦስተኛ ስብሰባ በአንድ ሳምንት ልዩነት ውስጥ በንግድ ሕጉ ድንጋጌ መሠረት መጠራት አለበት፡፡
አንቀጽ ሃያ ሶስት
የጉባኤው ተሳታፊዎች መመዝገቢያ ሠነድ
- በእያንዳንዱ ጉባዔ ላይ ባለአክሲዮኖች በጉባዔው ላይ መገኘታቸውን የሚያስረዳ የተሳታፊዎች መመዝገቢያ ሰነድ መኖር አለበት፤ ሰነዱም በስብሰባው የተገኙትን ወይም ወኪል የላኩትን ባለአክሲዮኖች ስምና አድራሻቸው፣ እያንዳንዱ ባለአክሲዮን ያለውን የአክሲዮን መጠንና የሚሰጠውን የድምፅ ቁጥር የሚያሳይ ዝርዝር መያዝ አለበት።
- የተሳታፊዎች መመዝገቢያ ሠነድ በስብሰባው መጀመሪያ ላይ በጉባዔው በአካል የተገኙ ባለአክሲዮኖች ወይም ወኪሎች የፈረሙበት ስለመሆኑ በማኅበሩ ጸሐፊ መረጋገጥ አለበት።
80
አንቀጽ ሃያ አራት
ድምጽ አሰጣጥ እና ወኪል መሰየም
1. አንድ ባለአክሲዮን ወኪሉን ለመሰየም ከስብሰባው 3 ቀን በፊት በማህበሩ ዋና ጽ/ቤት ተገኝቶ ውክልና ሊሰጠው ይገባል፡፡
- የውክልና አይነት፣ ስራው የሚከናወንበት ቦታ እና ሰዓት የሚመለከቱት ዝርዝር ሁኔታዎች በጥሪው ላይ ሊገለፁ ይገባል፡፡
- የባለ አክሲዮኖች ወኪሎች የሚኖራቸው ድምጽ የመስጠት መብት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚወጡ መመሪያዎች መሠረት ይወሰናል፡፡
አንቀጽ ሃያ አምስት
የጥቅም ግጭት
- ማንኛውም ባለአክሲዮን ስለራሱ ወይም ሶስተኛ ወገን ወክሎ ከማህበሩ ጋር የጥቅም ግጭት በሚያስነሱ ጉዳዮች ላይ ድምጽ መስጠት አይችልም፤
- በተለይም የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት ባለአክሲዮን ቢሆኑም የራሳቸውን ኃላፊነት፤ ተጠያቂነት እንዲሁም በማህበሩ እና በራሳቸው ጥቅም መካከል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግጭት የሚያስነሱ ጉዳዮች ላይ ድምጽ መስጠት አይችሉም፤
- በዚህ አንቀጽ ን/አንቀጽ 1 እና 2 መሰረት ድምጽ የመስጠት መብት የሚያሰጡ አክሲዮኖች ቢሆኑ የጉባዔውን ምልዓተ ጉባኤ መሟላት አለመሟላቱን ለመወሰን ቁጥር ውስጥ ይገባሉ፤
- በዚህ አንቀጽ ን/አንቀጽ 1 እና 2 የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ድምጽ ከመስጠት መቆጠብ የነበረባቸው ባለአክሲዮኖች ድምጽ በመስጠታቸው ምክንያት የማህበሩን ጥቅም የሚጻረር ውሳኔ ከተላለፈ በንግድ ሕግ አንቀጽ 391 መሰረት ውሳኔውን መቃወም ይቻላል።
አንቀጽ ሃያ ስድስት
ቃለ ጉባኤ
- የጉባዔ ውይይት በቃለ ጉባዔ መያዝ አለበት፤ ቃለ ጉባዔው በስብሰባው ላይ በተገኙት ዳይሬክተሮች እና በማህበሩ ፀሐፊ ከተፈረመበት በኋላ በቃለ ጉባዔ መዝገብ ይገለበጣል፤ ቃለ ጉባዔው ወደ መዝገብ በትክክል ስለመገልበጡ በማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወይም በሌሎች ሁለት የቦርድ አባላት መረጋገጥ አለበት።
- በዚህ አንቀጽ ን/አንቀጽ 1 ስር የተመለከተው ቢኖርም ጉባዔው ሥራ ከመጀመሩ በፊት ስብሰባው ላይ ከተገኙት ባለአክሲዮኖች መካከል በጉባዔው ላይ የተደረገው እና የተላለፈው ምትክ የሚፈርሙ ሶስት ባለአክሲዮኖችን መምረጥ ይቻላል፤ እንዲህ ዓይነት ምርጫ በአጀንዳ ባይካተትም ሊከናወን ይችላል፡፡
የጉባኤው ቃለ ጉባኤዎች በተለይ ከዚህ በታች የተመለከቱትን ጉዳዮች መያዝ አለባቸው ፡-
ሀ. የጉባኤውን ጥሪ አደራረግ፤
81
ለ. የስብሰባውን ቦታና ቀን
ሐ. አጀንዳዎቹን፤
መ. በጉባኤው የተገኙ የቦርድ አባላትን ስም፤
ሰ. በስብሰባው ላይ የተገኙ አክሲዮኖችን ብዛትና የምልዓተ ጉባኤውን ቁጥር፤
ረ. ለጉባኤው የቀረቡ ሰነዶች፤
ሸ. የውይይቱን አጭር ቃልና ውሳኔ ወይንም ማጠቃለያ፤
ቀ. የተሰጡትን ድምጾች ውጤት እና፤
በ. ጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች፤
3. ምልዓተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ምክንያት ጉባኤው ለመሰብሰብ ሳይችል የቀረ እንደሆነ የጉባኤው ሰብሳቢ ይሄው በቃለ ጉባኤ እንዲያዝ ያደርጋል፡፡
4. የቃለ ጉባዔ ቅጂዎች ወይም በአጭር የተዘጋጁ ግልባጮች ተቀባይነት የሚኖራቸው በዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ወይም በስብሰባው ላይ በተገኙ ሁለት የቦርድ አባላት ትክክለኛነታቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡
አንቀጽ ሃያ ሰባት የመደበኛ ጉባኤ ሥልጣን
- የማህበሩን የሀብትና ዕዳ ሒሳብ መግለጫ፤ የትርፍና ኪሣራ ሒሳብ እንዲሁም የዳይሬክተሮች ቦርድን ሪፖርት፣ የኦዲተሮችን ሪፖርት ካለም የተቆጣጣሪ ቦርዱን ሪፖርት አዳምጦ የማሻሻል ወይም የማጽደቅ፤ ወይም ያለመቀበል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በትርፍ አመዳደብና አከፋፈል እንዲሁም በአጠቃላይ ያለፈውን የሒሳብ ዓመት ማጠቃለያ የተመለከቱ የሒሳብ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የማሳለፍ፤
- ጉባኤ ዳይሬክተሮች እና ኦዲተሮች ይሾማል ወይም ይሽራል፣ የአገልግሎት ክፍያቸውን ይወስናል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማሻሻያ ያደርጋል
- ማህበሩ የግዴታ ወረቀቶችን እንዲያወጣ የመፍቀድ እንዲሁም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማህበሩ ስለሚሰጠው መያዣ የመወሰን፤
- በአንድ ጊዜ ወይም የመጀመሪያው ሽያጭ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተለያየ መጠን ከማህበሩ ሀብት ሃምሳ አንድ በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነውን መጠን ማስተላለፍ የተፈለገ እንደሆነ ይህን የመፍቀድ፤ እና
- በዚህ ሕግ ለአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በግልጽ ተለይተው ከተሰጡት ጉዳዮች በስተቀር በሌሎች የማህበሩ ጠቅላላ ጉባዔ በሚወስንባቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉ ውሳኔ የመስጠት፡፡
82
አንቀጽ ሃያ ስምንት
ውሣኔ ለማሳለፍ መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች
- ማንኛውም ጉባዔ ውሳኔ ማሳለፍ የሚችለው ምልዓተ ጉባዔው የተሟላ ሲሆንና በጉባዔው ከተገኙት ባለ አክሲዮኖች የአብላጫውን የድምጽ ድጋፍ ሲያገኙ ነው፡፡
- ለሚተላለፉት ውሳኔዎች መሟላት ያለበት ምልዓተ ጉባዔ የሚሰላው የማህበሩን ዋና ገንዘብ (ካፒታል) ካቋቋሙት አክሲዮኖች አንፃር ሆኖ ለእያንዳንዱ የጉባዔ ዓይነት በዚህ መመሥረቻ ጽሑፍ በተወሰነው መሠረት ነው፡፡ በሚካሄዱ ጉባዔዎች ሁሉ አስፈላጊው ምልዓተ ጉባዔ የሚታሰበው በሕግ መሠረት ድምጽ መስጠት መብት የሌላቸው አክሲዮኖች ከተቀነሱ በኋላ ቀሪዎቹ አክሲዮኖች በማኅበሩ ዋና ገንዘብ ውስጥ ባለቸው ድርሻ ወይም መዋጮ መሠረት ነው፡፡
አንቀጽ ሃያ ዘጠኝ
የመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ድምጽ አሰጣጥ እና ውሳኔ
- መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚጠራበት ጊዜ ድምጽ የመስጠት መብት ካላቸው ውስጥ 25% ካልተገኙ ወይም ካልተወከሉ ውሳኔ አይተላለፍም፡፡ ምልዓተ ጉባኤ ካልተሟላ የሁለተኛው ስብሰባ ጥሪ ይደረጋል፡፡
- መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለሁለተኛ ጊዜ በሚጠራበት ጊዜ ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸው ባለ አክሲዮኖች ቁጥር ሳይገደብ ስብሰባው ተደርጎ ውሳኔ ይተላለፋል፡፡
- የጉባዔው ውሳኔዎች የሚተላለፉት በጉባዔው ከተገኙት ድምፅ የመስጠት መብት ካላቸው አክሲዮኖች አብዛኛውን ካፒታል በሚወክሉት ድምፅ ከተደገፉ ነው፤ ለድምፅ ብልጫ አቆጣጣር ድምፅ ያልተሰጠባቸውም ሆነ ድምፅ ያልተጻፈባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከግምት ውስጥ አይገቡም፡፡
አንቀጽ ሰላሣ
ስለ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ድምጽ አሰጣጥ እና ምልዓተ ጉባዔ
- የማህበሩን ዜግነት ለመቀየር ወይም በተቋሙ ውስጥ ባለ አክሲዮኖች ያላቸውን ኢንቨስትመንት ለመጨመር በሚፈለግበት ጊዜ ሁሉም ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸው ባለ አክሲዮኖች ወይም
- የአስቸኳይ ጉባኤ ድምጽ አሰጣጥ እና ውሳኔን በሚመለከት ከላይ በንኡስ አንቀጽ አንድ ስር ከተመለከተው ውጭ በሌሎች ጉዳዮች ላይ 2/3ኛ ድጋፍ እንዲፀድቅ ይደረጋል፡፡
- በመጀመሪያው ጥሪ ድምጽ የመስጠት መብት ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ ቢያንስ የማኅበሩ ዋና ገንዘብ አንድ ሦስተኛ (1/3) የሚወክሉ ባለ አክሲዮኖች ወይም ወኪሎች የተገኙ እንደሆነ፤
- በሁለተኛው ጥሪ ድምጽ የመስጠት መብት ካላቸው አክሲዮኖች ውስጥ ቢያንስ የማኅበሩ ዋና ገንዘብ አንድ አራተኛ (1/4) የሚወክሉ ባለ አክሲዮኖች ወይም ወኪሎቻቸው የተገኙ እንደሆነ፤
83
-
- ሦስተኛው ጥሪ ድምጽ የመስጠት መብት ያላቸው አክሲዮኖ የሚወክሉት ዋና ገንዘብ (ካፒታል) ግምት ውስጥ ሳይገባ ባለ አክሲዮኖች ወይም ወኪሎቻቸው የተገኙ እንደሆነ ነው፡፡
- በሕግ ወይም በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ መሠረት በጉባዔው መተላለፍ የሚችሉ ውሳኔዎች በስብሰባው ላይ ባልተገኙ፤ ድምጸ ተአቅቦ ባደረጉ፤ በሀሳብ በተለዩ፤ ችሎታ በሌላቸው ወይም ድምጽ የመስጠት መብት በተከለከሉ ባለ አክሲዮኖች ላይ ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ ሰላሣ አንድ
የአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ሥልጣን
አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔው የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡-
- የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፍ የማሻሻል፤ የማህበሩን ዋና ገንዘብ የማሳደግ ወይም የመቀነስ፣
- የማህበሩን ዜግነት የመለወጥ፤
- ማህበሩ እንዲፈርስ፤ ወደ ሌላ ዓይነት የንግድ ማህበር እንዲለወጥ፣ እንዲከፋፈል ወይም እንዲዋሀድ የመወሰን፤
- ሌሎች በሕግ ወይም በመመስረቻ ጽሁፍ በዚህ ጉባዔ እንዲታዩ ተለይተው የተሰጡትን ጉዳዮች የመወሰን፤
- በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) ላይ የተመለከተው ቢኖርም የማህበሩን ባለአክሲዮኖች ስም፣ አድራሻ፣ ዜግነት፣ የያዙት የአክሲዮን ብዛትና የተከፈለውን የገንዘብ መጠን በተመለከተ የሚደረጉ ለውጦች የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፍ እንደማሻሻል አይቆጠሩም
አንቀጽ ሰላሣ ሁለት
የጉባዔው ውሳኔዎች ውጤት
- በንግድ ሕግ አነቀጽ 391 መሰረት ማንኛውም በውሳኔው ጥቅሙ የተጎዳ
ሰው በሕግና በማኅበሩ መመሥረቻ ጽሑፍ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመቃረን የተላለፈ ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግለት ውሳኔው መተላለፉን ካወቀበት ጊዜ አንስቶ ዘጠና (90) ቀናት ውስጥ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም ውሳኔው በንግድ መዝገብ የገባ ከሆነ ስለ ውሳኔው መተላለፍ በተጨባጭ አወቀም አላወቀም ውሳኔውን በመቃወም ለፍርድ ቤት ማመልከት የሚችለው ውሳኔው በንግድ መዝገብ ከገባበት ቀን አንስቶ ባሉት ተከታታይ ስልሳ (60) ቀናት ውስጥ ብቻ ነው
- ከላይ በንኡስ አንቀጽ (1) ስር የተመለከተው የውሳኔ ገደብ በሶስተኛ ወገኖች ጥቅም ላይ አሉታዊ ውጤት እንዳያስከትል በቅን ልቦና ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
ምዕራፍ ሶስት
አንቀጽ ሰላሳ ሶስት
የማህበሩ አስተዳደር
ማህበሩ የሚከተሉት የሥልጣን አካላት ይኖሩታል፡
- የባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ
- የዳይሬክተሮች ቦርድ
- ዋና ስራ አስፈጻሚ
4 ኦዲተሮች
5. የማህበሩ ጸሐፊ
አንቀጽ ሰላሳ አራት
የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ሥልጣንና ተግባራት
- የማህበሩ ባለአክሰዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሁሉንም ባለአክሲዮኖችና ከባለአክሲዮኖች መብት ያገኙ ሰዎች የሚገኙበት ስብስብ ነው፡፡
- የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የማህበሩን ስራዎች የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ከፍተኛ የስልጣን አካል ሲሆን ከላይ የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅ ቁጥር እንዲሁም የተሻሻለውን የንግድ ህጉን መሰረት በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤው የሚከተሉትን ኃላፊነቶች ይወጣል፡፡
ሀ) መመስረቻ ጽሑፉ ላይ ማሻሻያ ማድረግ
ለ) የማህበሩን የንግድ አርማ የመቀየር
ሐ) የማህበሩን ካፒታል መቀነስ ወይም ማሳደግ
መ) የኩባንያውን ስራ ማቆም እና መፍረስ አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት
ሠ) ዳይሬክተሮችን መሾም እና መሻር፣ የአገልግሎት ክፍያቸውን መወሰን
ረ) የተላላፊ አክሲዮን ድርሻ ውሳኔ መስጠት
ሰ) በዳይሬክተሮች ቦርድ እና በኦዲተሮች የሚዘጋጁ የሒሳብ ሚዛኖች እና ሪፖርቶችን ገምግሞ ማጽደቅ
ቀ) የኩባንያውን ኦዲተሮች መሾም እና መሻር፣የአገልግሎት ዘመናቸውን እና የአገልግሎት ክፍያቸውን መወሰን፣ ማሰናበት
- በሕግ ወይም በሌላ ስምምነት ካልተወሰነ በስተቀር ባለአክሲዮኖች ፈቃዳቸውን ሳይሰጡ ከአክሲዮን ጋር ተያያዥ መብቶች ሊገፈፉ አይችሉም፡፡
85
አንቀጽ ሰላሳ አምስት
የማህበሩ ዳይሬክተሮች ሹመት
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ላይ የዳይሬክተሮች እድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የስራ ልምድ፣ የስልጣን ዘመን እና ዳግም ምርጫን አስመልክቶ የተደነገገው እና በንግድ ህጉ አንቀጾች 296፣ 297፣ 298፣317 እና 318 እንደተጠበቀ ሆኖ፤
- ማህበሩ በጠቅላላ ጉባዔው በተሾሙ ዘጠኝ (9) ዳይሬክተሮች ቦርድ ይመራል፡፡
- ዳይሬክተሮቹ በየ3 አመቱ የሚሾሙ ሆኖ በዚሁ አግባብ ለሶስት አመታት በስራ ላይ ይቆያሉ።
- ከላይ በተራ ቁጥር 2 የተጠቀሰዉ እንደተጠበቀ ሆኖ የቦርድ አባላት ለተጨማሪ የሥራ ዘመናት በድጋሚ ሊመረጡ ይችላሉ፡፡
- የንግድ ህጉና በዚህ አንቀጽ በንኡስ አንቀጽ 2 ላይ የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ ጠቅላላ ጉባኤው ዳይሬክተሮችን የማሰናበት ስልጣኑ እንደተጠበቀ ነው፡፡
- ለኩባንያዉ የሚከተሉት ዘጠኝ የቦርድ አባላት ይኖሩታል፣
|
ተ/ቁ |
የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት |
|
1 |
አቶ ሸዋፈራዉ ደሳለኝ መስፍን |
|
2 |
አቶ ምስጋናዉ አብዲሳ ዲሲሳ |
|
3 |
አቶ ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ |
|
4 |
ዶ/ር ተገኔ ቢቂላ ጉራራ |
|
5 |
አቶ ኪሩቤል ከበደ ብርሃኑ |
|
6 |
ወ/ሮ ሀረጓ ወንድማገኝ አሰፋ |
|
7 |
አቶ መላኩ መንጂ ከ ራሞ |
|
8 |
አቶ አሊ ኑሪዬ ንጉሴ |
|
9 |
አቶ ተስፋዬ ፈለቀ ወልደሀና |
አንቀጽ ሰላሳ ስድስት የዳይሬክተሮች ቦርድ ስልጣንና ኃላፊነት
የዳይሬክተሮች ቦርድ አግባብነት ባላቸው ሕጎች እና በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት የሚሰጡ ሥልጣንና ተግባራት አሏቸው፡፡
በአጠቃላይ የዳይደሬክተሮች ቦርድ የሚከተሉት ስልጣንና ኃላፊነት አለባቸው፡-
- ቅጥር፣ ድጋፍ፣ ግምገማን እና ማካካሻን ጨምሮ የአመራር አፈጻጸምን ይቆጣጠራሉ ፤
- የማህበሩን ፋይናንስ የማስተዳደር፤ ማህበሩ በቂ ዋና ገንዘብ እና ክፍያዎችን በወቅቱ የመፈጸም አቅም ያለው መሆኑን የማረጋገጥ፤
- የማህበሩ አስተዳደራዊ አደረጃጀት የማህበሩን የፋይናንስ መግለጫዎችን እና ቁመናን ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን የማረጋገጥ፤
- የማህበሩን ለአደጋ ተጋላጭነት እና ውስጣዊ አሰራር ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂ የአሰራር ሥርዓት የመዘርጋት፤
- በማህበሩ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል፤ መከላከል ካልተቻለም ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ የመቀነስ፤
- የማህበሩ ባለአክሲዮኖች እና የቦርድ ስብሰባዎች ቃለ ጉባዔ፣ የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ፣ የዉጭ ኦዲተር ርፖርት፣ የዉስጥ ኦዲተር ርፖርት፣ የአክሲዮን መዝገብ ፅሃፊ በትክክል መመዝገቡንና መያዙን ማረጋገጥ; መከታተል።
7.የሒሳብ መዛግብት ለኦዲተሮች በአስፈላጊው ጊዜ ሁሉ እንዲቀርቡ የማድረግ፤
8. የፋይናንስ እንቅስቃሴን ያካተተ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔ የማቅረብ፤
9. በዚህ ሕግ ወይም በመመስረቻ ጽሁፉ መሠረት የማህበሩን ጉባዔዎች የመጥራት፤
10. የማህበሩ ዋና ገንዘቡ ¾ (ሦስት አራተኛ) በኪሣራ ባጣ ጊዜ ወዲያውኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የመጥራት፤
11.በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ፣ በዚህ መመስረቻ ጽሁፍ ወይም በባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት፤የማህበሩ ዕዳውን የመክፈል አቅም እየቀነሰ ከሄደ ወይም ዕዳውን መክፈል ካቋረጠ እንደነገሩ ሁኔታ ለጥንቃቄ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሥነ ሥርዓት፣ የማድረግ፡፡
12. ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲከፈቱ በማነጅመንት የቀረበዉን ጥናት ላይ ዉሳኔ መስጠት፣
13. የማህበሩን ዋና ቢሮ አድራሻ ለዉጥ እንደአስፈላጊነቱ ስታመን ዉሳኔ መስጠት፣
14.የማህበሩን የቦርድ አባላት የሚተዳደሩበት መተዳደሪያ ደንብ ማጽደቅ፣
15. አስፈላጊ ሆኖ ስገኝ ቦርዱ በአብላጫ ድምጽ ስወስን የማህበሩን ስራ በተሟላ መልኩ እንዲሰራ ለዋና ስራ አስኪያጅ ተጨማሪ የዉክልና ስልጣን መስጠት።
16. የጠቅላላ ጉባኤ ዉሳኔዎችን በሥራ ላይ እንዲዉሉ ማድረግ ።
አንቀጽ ሰላሳ ሰባት
የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ አሰጣጥ
- ከቦርዱ አባላት ውስጥ 51% ካልተገኙ ወይም ካልተወከሉ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ ማስተላለፍ አይችልም፡፡ ውሳኔዎችም በሙሉ አብላጭ ድምጽ ይተላለፋሉ፡፡
- በስብሰባ ላይ ያልተገኘ ዳይሬክተር በሚኖርበት ጊዜ በሌላ ዳይሬክተር የሚወከል ይሆናል ይሁን እንጂ በአንድ ጊዜ ለሁለት ሰው ወኪል መሆን አይችልም፡፡
- የቦርዱ ውሳኔዎች በቃለ ጉባኤ ተይዘው በስብሰባው ላይ በአካል ወይም በተወካይ በተገኙት የቦርድ አባላት እና በማኅበሩ ፀሐፊ መፈረም አለባቸው፤ ቃለ ጉባዔው ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ መዝገብ ውስጥ መቀመጥ አለበት፡፡
- የውሳኔዎቹ ኮፒዎች በሰብሳቢው እና በፀሐፊው ማጣራት ተደርጎባቸው እንዲፈረሙ ይደረጋል።
አንቀጽ ሰላሳ ስምንት
የዳይሬክተሮች የዋስትና አክሲዮኖች
ሁሉም ዳይሬክተሮች ኃላፊነት እና ግዴታቸውን በአግባቡ እና በትክክል ስለመወጣታቸው ዋስትና እንዲሆን ብር 165,000.00 (አንድ መቶ ስልሳ አምስት ሺ ብር/ ወይም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን የአይነት በዋስትና ያስይዛሉ፡፡ በዚህ መልክ የተያዘው ገንዘብ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባሉ የስራ ጊዜውን ጨርሶ ኃላፊነቱን እስኪያስረክብ ድረስ አይመለስለትም፡፡
አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ
ለማህበሩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ
- የአክሲዮን ማኅበሩ በዋና መሥሪያ ቤቱ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ ውስጥ የማኅበሩን የቦርድ አባላት የሥራ አስኪያጆችን፤ የተቆጣጠሪ የቦርድ አባላትን፤ ኦዲተሮችን፤ የማኅበሩ ፀሐፊዎችን እና በንግድ ሕጉ አንቀጽ 306 ንዑስ አንቀጽ 6 (ለ)፤ (ሐ) እና (ረ) መሠረት የተጠቀሱት ሰዎች የግል ሁኔታ ሞያቸውን፤ በሌሎች የንግድ ማኅበራት ወይም ድርጅቶች ያላቸውን ጥቅም፤ ሥራ፤ የቦርድ አባልነት ወይም ሌላ ኃላፊነት ካላቸው ይህንኑ እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች የሚያሳይ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ መያዝ አለበት፡፡ ዳይሬክተሩ የንግድ ማህበር የሆነ እንደሆነ የማኅበሩን ሥምና የዋና መሥሪያ ቤቱን አድራሻ ማሳየት አለበት፡፡
- ማናቸውም ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ ለማኅበሩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ላይ የሚመዘገቡ ዝርዝሮች እና ማስተካከያዎች በተመዘገበበት ወይም ከተስተካከለበት እለት አንስቶ ባሉት 15 (አስራ አምስት) ቀናት ውስጥ ለአክሲዮን ማኅበሩ ዋናው መሥሪያ ቤት እንዲላክ ይደረጋል፡፡
አንቀጽ አርባ
የዳይሬክተሮች ህጋዊ ተጠያቂነት
- ዳይሬክተሮች በሕግ፣ በመመስረቻ ጽሑፉ ወይም በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ስልጣንና ኃላፊነታቸውን በጥንቃቄ ሊወጡ ይገባል፡፡
- ዳይሬክተሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት በኩባንያው ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጉዳት በግል እና በቡድን ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡
- በግል እና በቡድን ኃላፊነት ያለባቸው ዳይሬክተሮች አጠቃላይ የማህበሩን ማኔጅመንት አስመልክቶ ግዴታቸውን በጥንቃቄ ሊወጡ ይገባል፡፡
- ከላይ በተመለከተው አግባብ ዳይሬክተሮቹ ያለባቸውን የግል እና የቡድን ኃላፊነት ሳይወጡ ቢቀር ወይም አስቀድሞ አውቀውት ሊከላከሉት የሚችሉትን ጉዳት ባለመከላከላቸው ምክንያት ማህበሩ ላይ ጉዳት ቢደርስ ወይም ማህበሩ ኪሳራ ላይ ቢወድቅ ተጠያቂ ይሆናሉ።
አንቀጽ አርባ አንድ
የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ስለመተካት
- በአንድ የበጀት ዘመን ውስጥ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ዳይሬክተር ከስራው በሚለቅበት ጊዜ የተቀሩት ዳይሬክተሮች የስልጣን ዘመኑን እንዲያጠናቅቅ በተጠባባቂ ዕጩ የቦርድ አባል እንዲተካ ይደረጋል፡፡
- ከዚህ በላይ በተመለከተው አግባብ ተሰናባች ዳይሬክተርን በተጠባባቂ የቦርድ አባል የመተካቱ ሂደት ለቀጣይ ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ ማረጋገጫ ይሰጥበታል፡፡ እንደየሁኔታው ጠቅላላ ጉባኤው ተተኪውን ሊያፀድቅ ወይም በሌላ ሰው እንዲተካ ሊወሰን ይችላል፡፡ ከላይ በንኡስ አንቀጽ አንድ ስር በተመለከተው አግባብ ተተኪዎቹ የሚያከናውኗቸው ሥራዎች አስመልክቶ ጠቅላላ ጉባኤ ሹመታቸውን ባያፀድቅም ህጋዊ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
- የቀሩት የቦርድ አባላት ቁጥር ከጠቅላላው የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ቁጥር ከግማሽ በታች የሆነ እንደሆነ የቀሩት አባላት የጎደሉትን ለመሾም አባላቱ ከጎደሉበት ጊዜ ጀምሮ በሠላሣ (30) ቀናት ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔውን መጥራት አለባቸው፤
አንቀጽ አርባ ሁለት
የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ
- የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ መሆን የሚቻለው ባለአክሲዮን የሆነ ዳይሬክተር ነው፤ በማህበሩ የዕለት ተዕለት ስራ (ኤክስክዩቲቨ) አመራር የሚሳተፍ ዳይሬክተር የቦርድ ሰብሳቢ መሆን አይችልም።
- የዳሬክተሮች ቦርድ በራሱ የተመረጠውን ሰብሳቢ ወይም ምክትል ሰብሳቢ በማንኛውም ጊዜ መሻር ይችላል፡፡
አንቀጽ አርባ ሶስት
የዳይሬክተሮች ቦርድ ም/ሰብሳቢ
የዳይሬክተሮች ቦርድ ም/ሰብሳቢ የዳይሬክተሮች ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በማይገኝበት ወቅት የዋና ሰብሳቢውን ሃላፊነት በሙሉ ተክቶ ይሰራል።
አንቀጽ አርባ አራት
የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ስልጣንና ኃላፊነት
- የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ የኩባንያውን የዕለት ተዕለት አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በበላይነት ይመራል፤ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በኃላፊነት ይፈጽማል፤ ተቋሙን ከሶስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረግ ግንኙነት ተቋሙን ይወክላል፤
- ከቦርድ የተሰጠዉን መሰረታዊ የኩባንያዉን ስራ ይሠራል ይጠብቃል ይቆጣጠራል፤
3.ኩባንያውን በመወከል በኩባንያው ስም እንዲሁም በመመስረቻ ጽሁፍ ላይ የተመለከቱ የንግድ አላማዎችን ለማሳካት ተገቢ ስራዎችን ያከናውናል፡፡
4.በሶስተኛ ወገን ዘንድ የሚደረግ ግንኙነቶች ማህበሩን በመወከል ቀርቦ ይፈጽማል ያስፈጽማል፡፡
5.የኩባንያውን አካውንት አያያዝ አስመልክቶ መመሪያ ይሰጣል፣ ቁጥጥር ያደርጋል፤
6.የማኔጅመንት ስብሰባዎችን ይጠራል፤ እንዲሁም የኩባንያውን የዕለት ተዕለት ተግባራትን ያከናውናል፡፡
7.በንግድ ህግ፣ በመመስረቻ ጽሑፍ እንዲሁም የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በሚያጸድቀው አግባብነት ባላቸው ህጋዊ ማዕቀፎችና አሰራሮች የኩባኒያውን መጠባበቂያ ሒሳቦች ያደራጃል፡፡
8.በመመስረቻ ጽሁፉ የተሰጠውን ስልጣን ለሌላ የኩባንያው ሰራተኛ በውክልና ያስተላልፋል፡፡
9.የኩባንያው ጥቅም መሠረት አድርጎ የኩባንያውን ህጋዊ ወኪሎች፣ የህግ ባለሙያዎች ወይም ሌሎች ባለሙያዎች ይሾማል፣ ዉክልና ይሰጣል።
10.ለቦርዱ አስቀድሞ በማሳወቅ በኩባንያዉ ስም ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ይከፍታል ያንቀሳቅሳል፤
11.ልዩ ልዩ ቼኮች፣ የገንዘብ ልውውጥ ደረሰኞች፣ የቃል ኪዳን ሰነዶች እና የክፍያ ሰነዶችን ይቀበላል፣ ይፈርማል፣ ይመነዝራል፣ በነዚህ ሰነዶች ላይ ድርድር ያደርጋል እንዲሁም የወጪ እና ገቢ እቃዎች ዲክላራሲዮኖች ላይ ይፈርማል፡፡
12 ለቦርዱ በቅድሚያ በማሳወቅ ኩባንያው ለሚያጋጥመው ኪሳራ፣ ጉዳት፣ አደጋ፣ ሪስክ እና ህጋዊ ተጠያቂነት ህጋዊ ኢንሹራንስ ሽፋን ይገዛል፡፡
13በጉዳዩ ላይ በቅድሚያ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማድረግ እና የማህበሩን ዓላማ መሠረት በማድረግ ትርፍ የሆነ ገንዘብን ኢንቨስት ያደርጋል።
- ለማህበሩ አስፈላጊ የሆኑ ሠራተኞችን የመቅጠር የማስተዳደር፣ ማሳደግ እና የማሰናበት ኃላፊነት አለበት፡፡
- የብድር ዉል፣ የግዢ ዉል፣ የቤት ክራይ ዉል እና ሌሎች ህጋዊ ዉሎችን ማህበሩን ወክሎ ይዋዋላል፣
- ማህበሩ ለመስራት በህግ ተፈቀደዉን አዳዲስ አገልግሎቶችን ያዘጋጃል፣ በንግድ ሰንሰለት ዉሥጥ ምርታማነት እንዲጎለብት ይሰራል፡፡
- የደንበኞችን እርካታ እና ታማኝነት እንዲጨምር ይሰራል፣
- የኩባንያዉ ቅርንጫፍ ኔትወርክ በታቀዱ ክልሎች መስፋፋቱን ይቆጣጠራል፤እርሱን ተክቶ ይህንን ስራ እንዲከታተል ኃላፊነት ሊሰጥ ይችላል።
- ከአበዳሪዎች ከለጋሾች ከቴክኒክ ባለሙያዎች ከማዕከላዊ ባንክ ኃላፊዎች እና ከግብር ባለስልጣኖች ጨምሮ ሌሎች ከማህበሩ አጋሮች ጋር ያሉ ግንኙነቶች ያጎለብታል።
- በየሩብ አመቱ የተከናወኑ የስራ ይዘቶችን ለቦርዱ ርፖርት ያደርጋል፡፡
- ሌሎች ቦርዱ በኃላፊነት የሚሰጠዉን የስራ አቅጣጫ ተግባራዊ ያደርጋል።
አንቀጽ አርባ አምስት
የማህበሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ስልጣንና ኃላፊነት
- ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው ከዋና ስራ አስፈፃሚ ጋር በቅርበት ይሰራል፤ በንግድ ልማት አስተዳደር ላይ ይሰራል፤የተቋሙን ቃጣይነት ያለው እድገትና ትርፋማነት ለማረጋገጥ በስትራቴጅካዊ ውሳኔ ላይ ይሳተፋል፡፡
- ከላይ በንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል።
- በዳይሬክተሮች ቦርድ ከተገለጸው ስትራቴጂ እና የንግድ እቅድ ጋር በማጣጣም ተቋሙን ለማሳደግ ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ያግዛል።
የተቋሙን ግቦች ለማሳካት የታዩ መሻሻሎችንና የተገኙ ውጤቶችን ሪፖርት ያደርጋል፡፡
-
- ከኩባንያው ተልዕኮ እንድሁም ከጥሩ የአደጋ አስተዳደር ልምዶች ጋር በማጣመር ኩባንያው ተጨባጭ፣ተጨባጭ፣ ጠንካራ እና ትርፋማ እድገትን እንድያስመዘግብ የኩባንያውን የንግድ እድገት ያደራጃል እና ያንቀሳቅሳል።
የንግድ አፈጻጸምን ለማሻሻል እድሎችን በእነዚህ መንገዶች ይለያል፡-
• አዳዲስ አገልግሎቶችን ያዘጋጃል
• የአገልግሎት መስጫ መንገዶችን ያሰፋል
• የደንበኞችን እርካታ እና ታማኝነት የጨምራል
• በንግድ ሰንሰለት ውስጥ ምርታማነትን ያጎለብታል
-
- የኩባንያው ቅርንጫፍ ኔትወርክ በታቀዱ ክልሎች መስፋፋቱን ይቆጣጠራል።
- በኩባንያው ውስጥ ላሉ ቁልፍ ሰራተኞች ሙያዊ እድገት አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡
- ከአበዳሪዎች፣ ከለጋሾች፣ ከቴክኒክ አቅራቢዎች፣ ከማዕከላዊ ባንክ ኃላፊዎች እና ከግብር ባለሥልጣኖች ጨምሮ ከዋና አጋሮች ጋር ያሉ ግንኙነቶችን ያጎለብታል፣ ያጠናክራል ።
አንቀጽ አርባ ስድስት ኦዲተሮች
- የማህበሩ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የማህበሩን ኦዲተር ወይም ኦዲተሮችን ይሾማል፡፡ የኦዲተሮች ሹመት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቀርቦ መፅደቅ አለበት፡፡
- የሚሾሙት ኦዲተሮች ወይም ህጋዊ ሰውነት ያላቸው እና ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ይሆናሉ፡፡
- የኦዲተሮች ተግባር እና ኃላፊነት በኢትዮጵያ ንግድ ህግ አንቀጽ 345 እስከ 355 በማይክሮ ፋይናንስ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እንዲሁም በተሸሻለው አነስተኛ የፋይናንስ ስራ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1164/2012 መሰረት እና አግባቢነት ባለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት ይሆናል፡፡
- ኦዲተሮች በሥራ ላይ የሚቆዩት በፈራሚዎች ጉባዔ የተመረጡት የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባዔ እስከሚደረግ ድረስ ይሆናል፤
- ኦዲተሮች ሥራቸውን በሚሠሩበት ጊዜ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን አነስተኛ የኦዲት መመዘኛውን ማሟላትና የንብረት ግምትና ኃላፊነትን በሚመለከት ሪፖርታቸው ሊሸፍን ይገባል፡፡
- የዓመቱ የሂሳብ ዓመት በተጠናቀቀ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ የኦዲት ሪፖርቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መላክ አለበት፡፡
አንቀጽ አርባ ሰባት
የማህበሩ ፀሐፊ
- የአክሲዮን ማኅበሩ ፀሐፊ ሊኖረው ይገባል፤ የፀሐፊው ቅጥርና ስንብት በሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት በቦርድ የሚጸድቅ ይሆናል፡፡
- የማኅበሩ ፀሐፊ ተጠሪነቱ ለሥራ አስኪያጁ ይሆናል፡፡ ፀሐፊው አግባብነት ባላቸው ሕጎች የሚያከናውናቸው ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፡፡
- በንግድ ህግ አንቀጽ 341 መሠረት :-
1) የማህበሩን መረጃዎችና መዛግብት የማደራጀትና የመያዝ ፣
2) ለሚመለከተዉ አካል ሪፖርቶችንና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በወቅቱ የመስጠት ፣
3) ለባለአክሲዮኖችና ለሦስተኛ ወገኖች መረጃ መስጠት፣
4) የባለአክሲዮኖች እና የቦርድ አባላትን ስብሰባ ማዘጋጀት።
5) ቃለ ጉባኤዎችን የማዘጋጀት እና አደራጅቶ የመያዝ ፣
6) በስራ አስኪያጁ እና በማህበሩ መመስረቻ ፅሁፍ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራትን የማከናወን።
7) ማህበሩን ከተለያዩ አፍራሽ ተግባራት ህግንና መመሪያን ፖሊሲን መሰረት አድርጎ የመከላከል እና የመጠበቅ፤
8) ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም የማህበሩ ፀሀፊ በዚህ ህግ ወይም በመመስረቻ ፅሁፍ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ በማህበሩ ባለአክሲዮኖች ወይም በሦስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰዉ ጉዳት ኃላፊ ነዉ።
ምዕራፍ አራት
አንቀጽ አርባ ስምንት
የሂሳብ አያያዝና ፋይናንስ አጠቃላይ ድንጋጌ
የሂሳብ መዛግብት እና ሰነዶችን መያዝ በተመለከተ በማይክሮ ፋይናንስ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እንዲሁም በተሸሻለው አነስተኛ የፋይናንስ ስራ አዋጅ ቁጥር 1164/2012 እና በኢትዮጵያ ንግድ ህግ ላይ የተደነገጉት በማህበሩ ሂሳብ መዛግብት ላይ ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል።
አንቀጽ አርባ ዘጠኝ
የሂሳብ ሰነዶች እና መረጃዎች
ኩባንያው የንግድ እንቅስቃሴዎችን እና የፋይናንስ አቋሙን በግልጽ በሚያሳይ መልኩ አስፈላጊ የሂሳብ ሰነዶችን ያዘጋጃል ይህም አግባብነት በአላቸው የንግድ ህጉ አንቀጾችና በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እንዲሁም በተሸሻለው አነስተኛ የፋይናንስ ስራ አዋጅ ቁጥር 1164/2012 መሰረት ይሆናል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ የፋይናንስ ሪፖርት
- የኩባንያው የሒሳብ አመት እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ይጠናቀቃል፡፡ ሆኖም የመጀመሪያው የስራ ዘመን ኩባንያው ከተመዘገበበት እለት አንስቶ እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ይሆናል፡፡
- የአመታዊ የፋይናንስ ሪፖርቱ በዳይሬክተሮች ቦርድ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የኩባንያውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያሳይ እና ለባለ አክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርብ ሪፖርት ነው፡፡
- ይህ ሪፖርት የትርፍ እና ኪሳራ ዝርዝር መረጃ፣ የዳይሬክተሮች እና የኦዲተሮች የአገልግሎት ክፍያ፣ የትርፍ ክፍፍል ዝርዝር ሃሳቦችን በውስጡ ያካትታል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-አንድ
የሒሳብ ሠነዶችንና ሪፖርቶችን ስለመስጠት
ጠቅላላ ጉባዔው ጥሪ ከሚደረግበት ቢያንስ ከ40 ቀናት በፊት የማኅበሩን የንብረት ዝርዝር፤ የሀብትና ዕዳ ሒሳብ መግለጫ፤ትርፍና ኪሣራ መግለጫ እና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ለኦዲተሮች እና ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወይም አግባብነት ላለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት መተላለፍ ይኖርበታል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-ሁለት
የሂሳብ ሚዛን፣ ትርፍና ኪሳራ መግለጫ
የሂሳብ ሚዛን እንዲሁም የትርፍና ኪሳራ መግለጫ የሚከናወነው አግባብነት ባለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁም አግባነት ባላቸው ሕጎች መሰረት ይሆናል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-ሶስት
የካፒታል በተቀማጭ ገንዘብ እና ህጋዊ መጠባበቂያ
- ማህበሩ በንግድ ሕግና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት የካፒታል ተቀማጭ ገንዘቡን እና ህጋዊ መጠባበቂያውን ገንዘቡን ዘወትር አሟልቶ ሊገኝ ይገባል፡፡
- ማህበሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች እና በንግድ ህግ መሠረት የመጠባበቂያ ሂሳብ ይይዛል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-አራት
አገልግሎት፣ የእርጅና ዋጋ ቅናሽ እና አሞርታይዜሽን
- ተፈፃሚነት ባለው ህግ አክሲዮን ማህበሩ የንብረቶቹን የዋጋ ቅናሽ እና የካፒታል ወጪዎችን ስሌት ይይዛል፡፡
- ማህበሩ የንብረት የዋጋ ቅናሽ ስሌት የሚያከናወነው አግባብነት ባላቸው ህጎች፣ በአነስተኛ የፋይናንስ ሥራ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1164/2012 በሒሳብ አያያዝ እና አካውንቲንግ መርሆዎች አግባብ ይሆናል።
አንቀጽ ሃምሳ-አምስት
የፋይናንስ መግለጫ ህትመት
- ሒሳብ አመቱ ከተጠናቀቀበት እለት ቀጥሎ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ የተፈረመ ጊዜያዊ የሂሳብ ሚዛን እና የትርፍ እና ኪሳራ መግለጫ ኮፒዎች ተዘጋጅተው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲላኩ ይደረጋል፡፡
- ማህበሩ ኦዲት የተደረገውን የሂሳብ ሚዛን እና የትርፍ እና ኪሳራ መግለጫውን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ ላይ እንዲታተም ሊያደርግ ይችላል፡፡
ምዕራፍ አምስት
የማህበሩ መፍረስና ተያያዥ ጉዳዮች
አንቀጽ ሃምሳ-ስድስት
የኩባንያው በባለአደራ መተዳደርና የመፍረስ ሁኔታ
- አግባብነት ያላቸው የንግድ ህጉና የብሔራዊ ባንክ መመሪያው የኩባንያውን በአደራ መተዳደርና መፍረስን በተመለከተ ተፈፃሚነት አላቸው፡፡
- በአነስተኛ የፋይናንስ ስራ አዋጅ ቁጥር 626/2001 አንቀጽ 19 እንዲሁም በተሻሻለው አነስተኛ ፋይናንስ ስራ አዋጅ ቁጥር 1164/2012 ስር ከተመለከቱት ምክንያቶች አንዱ ወይም ከዚያ በላይ በሚኖርበት ጊዜ ኩባንያው በባለአደራ ተሿሚ ይተዳደራል፡፡
- በአነስተኛ የፋይናንስ ስራ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እንዲሁም በተሻሻለው አነስተኛ የፋይናንስ ስራ አዋጅ ቁጥር 1164/2012 እስካአልተቃረኑ ድረስ በንግድ ህጉ ላይ ስለ ባለአደራ አስተዳደርና ስለመፍረስ የተደነገጉት አንቀጾች ተፈፃሚነት አላቸው፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-ሰባት
ማህበሩ የሚቆይበት ዘመን
ማህበሩ ላልተወሰነ ጊዜ የተቋቋመ ሲሆን ተፈጻሚነት በአላቸው ህጎች እና በኢትዮጵያ ንግድ ህግ አንቀጽ 473 እና 474 መሰረት ማህበሩ ሊፈርስ ይችላል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-ስምንት
የማህበሩን የመመሥረቻ ጽሑፍ ስለማሻሻል
- በህግ እስካልተደነገገ ድረስ፣ በማህበሩ ባለአክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት መመስረቻ ጽሑፍ ሊሻሻል ይችላል፡፡
- በመመስረቻ ጽሑፍ ማሻሻያ ውሳኔ እንዲሰጥ የተጠራ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ስራዎቹን በመመስረቻ ጽሑፉ፣ በንግድ ሕጉ እና በአነስተኛ ፋይናንስ ሥራ አዋጅ ቁጥር 626/2001 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1164/2012 በተደነገገው መሠረት ሊያከናውን ይገባል፡፡
አንቀጽ ሃምሳ-ዘጠኝ
የሌሎች ህጎች ተፈፃሚነት
በዚህ መመሥረቻ ጽሑፍ ውስጥ ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን በሚመለከት የኢትዮጵያ ንግድ ህግ ቁጥር
1243/2013፣ አነስተኛ የፋይናስ ተቋማት አዋጅ ቁጥር 626/2001 እና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር
1164/2012 እና ሌሎች የሀገሪቷ ህጎች ተፈፃሚነት አላቸው፡፡
አንቀጽ ስልሳ
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
- የባለ አክሲዮኖች አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በማንኛውም ጊዜ በመመስረቻ ጽሁፉ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ ይችላል፡፡
- በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በተዘጋጀው መመስረቻ ጽሁፍ አተረጓጎም ላይ መጣረስ ሲያጋጥም የአማርኛ ሰነድ ተፈጻሚነት አለው፡፡
- ይህ መመሰረቻ ጽሁፍ በባለአክሲዮኖች ውይይት ከተረጋገጠና ከተፈረመ በኋላ በሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት ቀርቦ ከጸደቀበት ቀን አንስቶ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ማረጋገጫ
|
ተ/ቁ |
የማህበሩ ቦርድ አባላት ስም |
ፊርማ |
ቀን |
|
1 |
ሸዋፈራዉ ደሳለኝ መስፍን |
||
|
2 |
አቶ ምስጋናዉ አብዲሳ |
||
|
3 |
አቶ ጥላሁን ጉግሳ |
||
|
4 |
ወ/ሮ ሀረጓ ወንድማገኝ |
||
|
5 |
አቶ ኪሩቤል ከበደ |
||
|
6 |
ዶ/ር ተገኔ ቢቂላ ጉራራ |
||
|
7 |
አቶ አሊ ኑሪዬ |
||
|
8 |
አቶ መላኩ መንጂ |
||
|
9 |
አቶ ተስፋዬ ፈለቀ |
KEBRONHILL microfinance We will strengthen you and make it better in the future because it is a beautiful microfinance that is at a very good level.